ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ(ሊቀጳጳስ)

የትናንቱ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሃብተ ማርያም የዛሬው ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በጎንደር ክፍለ ሃገር ደብረ ታቦር አውራጃ በፋርጣ ወረዳ ልዩ ስሙ መገንታ ቁስቋም በተባለ ቦታ ከአባታቸው ከቄስ ወርቅነህ ትኩ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አንጓች አታሌ እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር በ 1916 ዓ.ም ተወለዱ። ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ልጆቻቸውን በማስተማር ከሚያምኑት ከአባታቸው ከቄስ ወርቅነህ ትኩ ፊደል ከመቁጠር ጀምሮ ንባብ እስከመለየት እና ዳዊት እስከመድገም ድረስ ተምረዋል። በዚሁ በሕጻንነት ዕድሚያቸው ከትውልድ ስፍራቸው አቅራቢያ በሚገኝው ድድም ጊዮርጊስ በተባለው ደብር ከመሪጌታ ወንድም በመሄድ ጸዋትዎ ዜማ አጠናቀው ከተማሩ በኋላ ይህኑ የቃል ትምህርት ለማጠናከር እና ለመከለስ አዛውር ኪዳነ ምሕረት ወደሚገኙት መሪጌታ ጀምበር ሄዱ። በዚያም የቃል ትምህርቱን ከነአመሉ ከለዩ በኋላ በ 1928 ዓ.ም በዝነኛው ደብር አትከና ጊዮርጊስ በመሄድ ከመሪጌታ ፈቃዱ ድጓ ተምረዋል።

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የቃል ትምህርትን፣ ጾመ ድጓን እና ድጓን አጠናቀው ከተማሩ በኋላ ሰዋስው የመለየት እና ቅኔ የመማር ልዩ ፍላጎት ስለነበራቸው ከተወለዱበት ስፍራ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ወደ ታላቁ ደብር ቆማ ፋሲለደስ በመሄድ ከመሪጌታ አምደ ብርሃን ሰዋስው ለይተዋል፤ ቅኔም ቆጥረው ተቀኝተዋል። በመቀጠልም በአማራ ሳይንት ገርት አቡነ አቢብ ከመሪጌታ አበበ ልዩ ልዩ የቅኔ መንገዶችን ከነአገባባቸው በመማር ቅኔ ለሁለተኛ ጊዜ ተቀኝተዋል።

ብፁዕነታቸው ከሚማሩት ትምህርት ባሻገር በ-1927 ዓ.ም ገና የ-11 አመት ልጅ እያሉ ማዕረገ ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ አብርሐም በደብረ ታቦር መድኃኔ ዓለም ከተቀበሉብት ጊዜ ጀምሮ ለትምህርት በተዘዋወሩባቸው አድባራት ሁሉ በዲቁና አገልግለዋል። ብዙም ሳይቆዩ ይህ አለም አልተገባቸውምና በ 1931 ዓ.ም ዓለሙን እና ምኞቱን ንቀው፣ እግዚአብሔርን መከተል እና ማገልገል እንደሚገባ አምነው በጣና ሕይቅ በምትገኘው ክርስቶስ ሰምራ ገዳም ምንኩስናን ተቀብለዋል። ከዚህም በኋላ ትርጓሜ መጻሕፍትን የመማር ልዩ ጉጉት ስለነበራቸው እስቴ መካነ ኢየሱስ ወንበር ዘርግተው ያስተምሩ ወደነበሩት ዝነኛው የትርጓሜ ሊቅ መምህር ወልደ ሚካኤል አቅንተው ጉባኤው በተስቦ በሽታ ምክንያት እስኪፈታ ድረስ ትርጓሜ ወንጌልን ተምረዋል። በእስቴ የተከሰተው ችግር ሳይበግራቸው እና የትምህርት ፍላጎታቸውን ሳያጠፋው ቅኔን ከነአገባቡ ወደተማሩበት ገርት አቡነ አቢብ በመሄድ ቅኔን እና መንገዱን በዚሁ ጉባኤ እንደገና አጥብቀዋል። ይሁን እንጂ መሪጌታ አበበ በግብርና የሚተዳደሩ በመሆናቸው ይበልጠውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት የግል ሥራቸውን በመሥራት ስለነበርና ጉባኤው ስለቀዘቀዘ ብፁዕነታቸው ጉባኤውን ለቀው መላ ጊዜያቸውን በትምህርት የሚያሳልፉበት ጉባኤ ፍለጋ ሊሄዱ ተገደዋል።

በጉባኤ ፍለጋ ብዙም ሳይንገላቱ ግሸን ደብረ ከርቤ ለመሳለም በሄዱበት እና ጸሎት በሚያደርጉበት ወቅት እግዚአብሔር በአንድ መነኩሴ ላይ አድሮ ቀጣዩ ጉዟቸው ገረገራ ጊዮርጊስ ወደሚገኙት ምትክ ወደማይገኝላቸው የትርጓሜ መምህር ወደ መምህር ሰይፈ ሥላሴ መሆን እንደሚገባው አመለከታቸው። ብፁዕነታቸውም ጥሪውን ተቀብለው ወደ መቄት ገረገራ ጊዮርጊስ በመሄድ የመምህር ሰይፈ ሥላሴ ደቀ መዝሙር ሆኑ። ቀለም ተቀባይ ከመሆናቸው የተነሳ በመምህራቸው ዘንድ ልዩ ተወዳጅነት ነበራቸው። ምንም እንኳን ብፁዕነታቸው ከተማ የመግባት ፍላጎት ባይኖራቸውም መምህራቸው ከአዲስ አበባ ጥሪ ስለደረሳቸው መምህራቸውም ብፁዕነታቸውን በመቄት ትተው የመሄድ ፍላጎት ስላልነበራቸው አብረዋቸው ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ ተግሳፅ የተቀላቀለበት ትዕዛዝ ሰጧቸው። በመሆኑም ብፁዕነታቸው የመምህራቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው በ-1937 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ገቡ። መምህር ሰይፈ ሥላሴ የአዲስ አበባ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ በመሆናቸው ጉባኤው በዚያው ተዘርግቶ ብፁዕ አባታቸን የመጻሕፍተ ሐዲሳትን እና የዳዊትን ትርጓሜ ምሥጢር አደላድለው ተምረዋል። ሆኖም መምህራቸው ብዙም ሳይቆዩ በሞት ስለተለዩ ጉባኤው እንዳይፈታ ደቀ መዛሙርቱም እንዳይበተኑ ብፁዕነታቸው የመምህራቸውን ቦታ ተክተው ትርጓሜ ሐዲሳትን አስተምረዋል። ይሁን እንጂ ችግር ስለበዛባቸው በማስተማሩ ሥራ ከአንድ አመት በላይ ሊቆዩ አልቻሉም። በዚህም የተነሳ ብፁዕነታቸው በአዲስ አበባ ተቀምጠው የመምህራቸው ወንበር ተፈትቶ ማየትን ስላልወደዱ ወደ ኢየሩሳሌም የመሄድ ፍላጎት አደረባቸው። ይህም ፍላጎታቸው ፈቃደ እግዚአብሔር ባለመሆኑ መጀመሪያ ቤተ ክህነቱ ባለመፍቀዱ በኋላም የአረቦች እና የእስራኤል የመጀመሪያው ጦርነት በመነሳቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሳይሄዱ ቀሩ።

የኢየሩሳሌሙ ጉዞ አለመሳካትን ተከትሎ ብፁዕ አባታች ዘመናዊ ትምህርት የመማር ፍላጎት ስላደረባችው ከዚያ በኋላ ላለው የአገልግሎት ሕይወታቸው መሠረት የሆነውን የጽሕፈትን እና የስብከትን ዘዴ ወዳጠኑበት ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተዋል። በዚሁ ትምህርት ቤትም ትምህርታቸውን በአመርቂ ሁኔታ እየተከታተሉ በተጓዳኝ በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በየሳምንቱ እሁድ የሃይማኖት ትምህርት በማስተማር፣ ለሕጻናት መጽሐፍ ቅዱስ በማስተማር፣ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ለበሽተኞች የማጽናኛ ትምህርት በመስጠት እና በቅድስት ሥላሴ አዳራሽ ሕዝብ በሚሰበሰብበት ወቅት ስብከት በመስበክ ሐዋርያዊ ተግባር አከናውነዋል። ከዘመናዊ ትምህርት በተጨማሪም በዚሁ ትምህርት ቤት በሚሰጠው የብሉያት ትርጓሜ ትምህርት ከመምህር ፊላታዎስ የስምንቱ ብሔረ ኦሪት፣ የአራቱን ዓበይት ነቢያት፣ እና የ-12ቱን ደቂቅ ነቢያት መጻሕፍት ትርጉም ተምረዋል። 

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በየዓመቱ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ከመሆናቸው የተነሳ ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ ወደ ሦስት ጊዜ ያክል ሽልማትን ለመቀበል ከመብቃታቸውም በላይ ከወዳጅ ቤተ ክርስቲያን በተገኘው ዕድል ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ለመማር ቁስጥንጥንያ ወደሚገኛው የግሪክ ኦርቶዶክስ ኢኩሜኒካል መንበረ ፓትርያሪክ ተልከው ልዩ ስሙ ሔልኪ በሚባለ የሥነ መለኮት ኮሌጅ ተምረው በዲግሪ ተመርቀዋል። የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ባለዲግሪ ካህን በመሆንም በ1949 ዓም ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።

ብፁዕነታቸው ምንም እንኳን የተማሩትን ሃገር በቀል ትምህርት በውጭ ሃገር እና ዘመናዊ በሆነ ትምህርት አጠናክረው ባለዲግሪ ሆነው ቢመለሱም በወቅቱ በቤተ ክህነቱ ውስጥ ስለዕውቀት፣ ስለለውጥ እና ስለዕድገት የሚያስብ ስላልነበረ ቤተ ክህነቱ እርሳቸውን ተቀብሎ ለማሠራት ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም ብፁዕነታቸው እና በውጭ ሃገር አብረዋቸው የተማሩ ጓደኞቻቸው ለንጉሠ ነገሥቱ ለጻፉት ደብዳቤ ምላሽ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተመድበው የተማሩትን በማስተማር ሥራ እንዲጀምሩ ተፈቀደላቸው። ከዚያም በ 1950 ዓም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ መልካም ፈቃድ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በመሆን ትምህርት ቤቱ የትምህርት ቤት መልክ እንዲኖረው ከማድረግ ጀምሮ መማሪያ መጻሕፍትን ራሳቸው በማዘጋጀት እንዲሁም መሪ ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው አስተማሪ ሆነው ትውልድ የማይረሳው ሥራ ሠርተዋል። 

በ-1952 ዓም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያን በአዲስ መልክ ለማራመድ ከነበራቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ልዩ ካቢኔ ሲያቋቁሙ ብፁዕ አባታችን ከ-12ቱ ክፍል የመንፈሳዊው ካቢኔ ኃላፊ ሆነው በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ ተመርጠው ተሾሙ። የዚህም ክፍል ዓላማ የንጉሠ ነገሥቱን ትዕዛዝ ተቀብሎ ማስተላለፍ፣ የሃይማኖት ተቋማትን መቆጣጠር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ችግር ከነመፍትሄው አጥንቶ ማቅረብ፣ ጳጳሳት እና እና የአድባራት አስተዳዳሪዎች በሚያስፈልጉበት ጊዜ ብቁ የሆኑ ሰዎችን ማቅረብ ነበር። በዚሁ በ-1952 ዓም መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴን ጨምሮ አንዳንድ አድባራት ያለ አስተዳዳሪ በመሆናቸው ብፁዕነታቸው ለአስተዳዳሪነት ብቁ ናቸው ያሏቸውን ሰዎች ለንጉሠ ነገሥቱ ሲያቀርቡ ግርማዊነታቸው ቅድስት ሥላሴ ለብፁዕነታቸው እንዲሚገባ ስላመኑ ብፁዕነታቸው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተጠባባቂ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ከአንድ አመት በኋላም ከነሙሉ ማዕረጉ ሊቀ ሥልጣናት ተብለው ተሾሙ። በአስተዳዳሪነት ዘመናቸው ያከናወኗቸው ተግባራት ቢጻፉ ብራና ሊሸከመው አይችልም። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል ቤተ ክርስቲያኑ በአስተዳደርም ሆነ በአገልግሎት ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ምሳሌ የሚሆን ነውና ካቴድራል አሰኝተውታል፤ በነበረው ሕንጻ ላይ ተጨማሪ ሥራ አሠርተዋል፤ በካቴድራሉ ውስጥ ብቃትን ብቻ መስፈርት ያደረገ የሰራተኞ ቅጥር ፈጽመዋል፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከጵጵስና ጀምሮ እስከ ፓትርያሪክ ድረስ የደረሱ አባቶችን በትምህርት ታንጸው እንዲወጡ አድርገዋል፤ በአጠቃላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የካቴድራሉን ክብር እና ሞገስ ለማስጠበቅ በትጋት ሠርተዋል።

ብፁዕነታቸው ሁለቱን ታላላቅ ኃላፊነቶች ማለትም የመንፈሳዊ ካቢኔ ኃላፊነትን እና የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪነትን እስከ 1966 ዓም ለ-14 ዓመታት በመሸከም ከፍተኛ የሥራ ውጤት አሳይተዋል። ከእነዚህ ሁለት ኃላፊነቶች በተጨማሪ በራሳቸው ተነሳሽነት እና በውጭ ሀገር ዕርዳታ በመላ ሃገሪቱ እየተዘዋወሩ ትምህርት ቤቶችን ከፍተዋል፤መጻሕፍትን ጽፈዋል፤ የትርጉም ሥራዎችን ሠርተዋል፥አሠርተዋል፤ ስብከተ ወንጌል በመገናኛ ብዙሃን በተለይም በብስራተ-ወንጌል ራዲዮ እንዲስፋፋ አድርገዋል፤ ልዩ ልዩ ድርጅቶችን አቋቁመዋል። ላበረከቷቸው ለእነዚህ ሃገራዊ፣ ሰብአዊ እና ሃይማኖታዊ አስተዋጽኦዎች ከሀገራችን እና ከውጭ ሀገራት በርካታ የክብር ሽልማቶችን እና አልባሳትን ተጎናፅፈዋል። ዋና ዋናዎቹም 

  • የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ባለ አምበል 1ኛ ደረጃ
  • የዳግማዊ ምኒልክ የክብር ኮከብ ባለ አምበል 1ኛ ደረጃ
  • የቅድሥት ሥላሴ ኒሻን የኮማንደር ደረጃ ያለ ፕላኩ 
  • የቅድሥት ሥላሴ ኒሻን የኮማንደር ደረጃ ከነ ፕላኩ

ልዩ ሽልማት፦

  • ከግሪክ መንግሥት
  • ከግሪክ ቤተ ክርስቲያን
  • ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን (በግሪክ)
  • የላዝሩስ ኒሻን ከኦስትርያ(ቪዬና)
  • ጥቄር ካባ ባለራስ ማዕርግ በሙካሽ የተሠራ፤
  • ቀይ ከፋይ ላይ ወርቅ የተጠለፈበት ካባ እንዲሁም በሙካሽ የተሰራ ቀሚስ
  • ከወርቅ የተሰራ የእጅ መስቀል ናቸው።

በ-1966 ዓም በሀገሪቱ በተነሳው የመንግሥት ለውጥ እንቅስቃሴ ከንጉሠ ነገሥቱ፣ ከመኳንንቱ እና ከመሳፍንቱ ጋር ስለዋሉ እና ስለሠሩ ብቻ ያለምንም ወንጀል እና ክስ ብፁዕነታቻው ለእስር ተዳርገዋል። የታሰሩበትንም ምክንያት እንኳን እርሳቸው አሳሪው ደርግም አያውቀውም ነበር። ማንም ተጠያቂ ሳይኖር ለመታሰርም የሚያበቃ ምክንያት ሳይኖር ብፁዕነታቸው በእስር ቤት ከ8 አመት በላይ ቆይተዋል። ይህም የግፍ እስር ከሚወዱት ሥራቸው እና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ይለያቸው እንጂ ከክርስቶስ ፍቅር እንዲሁም ከስብሐተ እግዚአብሔር እና ከሐዋርያዊ ተግባር ሳያግዳቸው ኖሯል። አብረዋቸው የታሰሩትን በእግዚአብሔር ቃል በማጽናናት፣ ስብሐተ እግዚአብሔርን ሳያቋርጡ በማድረስ፣ መጻሕፍትን በመድረስ፣ ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን በማጥናት አሳልፈውታል። የእስር ቤቱን ዘመን ሲገልጹት “እስር ይባል እንጂ እግዚአብሔር ሊጠብቀኝ ያደረገው ነው” ይሉታል። አብረዋቸው በእስር ያሳለፉት ስለብፁዕነታቸው ሲናገሩ ደግሞ “እግዚአብሔር ለእኛ መጽናኛ ይሆኑ ዘንድ የሰጠን የመጽናናት አባታችን” ይሏቸዋል። በዚህ የሰቆቃ ዘመን እንኳን የታሰረው ያልታሰረው ሁሉ ቀሚሱን እና ዳዊቱን በፍርሃት ሲያስረክብ ብፁዕነታቸው ግን በምንኩስናቸው እና በክብራቸው የመጣውን ነገሩ ሁሉ አንዳች ሳይቀበሉ አይደለም ዳዊት እና ቀሚስን ማስረከብ ቀርቶ የራስ ጸጉራቸውን እንኳን አንዷን ሳያስነኩ ቆይተዋል። ንጉሠ ነገሥቱን ጨምሮ ታላላቅ ምንስቴሮች፣ መኳንንት፣ መሳፍንት እንዲሁም ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ቅርበት አላቸው የተባሉት ሁሉ ሲረሸኑና ሲገደሉ እርሳቸውን ግን ረድኤተ እግዚአብሔር ጠብቋቸው ከስምንት አመት በኋላ ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት አሳሪው ክፍል “ለአብዮቱ እንቅፋት ይሆናሉ በማለት በጥርጣሬ ታስረው ነበር፤ አሁን ግን በምሕረት ተፈተዋል” በሚል ስላቅን ባዘለ ማስረጃ ምሕረት የማያውቀው ምሕረት አድራጊ መስሎ ከእስር ፈቷቸዋል። 

ብፁዕ አባታችን ከእስር ቢፈቱም በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ በደርግ አገዛዝ ስር ወድቃ ስለነበር በቤተ ክህነቱ ዙሪያ ያሉት ሠራተኞች ብፁዕነታቸውን ሊያቀርቧቸው እና ሥራ ሊያሠሯቸው ፈቃደኛ አልነበሩም። ሆኖም ግን ብፁዕነታቸውን በሥራ ትጋታቸው የምታውቃቸው የኦስትሪያ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብታሠራቸው እና ዕውቀታቸውን እና የሥራ ክህሎታቸውን ብትጠቀምበት መልካም እንደሆነ ካልሆነ ግን በተወካያቸው አማካኝነት የውጭ ዕድል እንደምትሰጣቸው ሲሰማ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እንዲሠሩ ተፈቀደላቸው። በዚህ ትምህርት ቤትም ለተወሰነ ጊዜ እንደሠሩ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የነበረውን የስራ ሁኔታ ስላልወደዱት ወደ ማተሚያ ድርጅት ተዛውረው በዚያ ለትውልድ ጠቃሚ የሆኑ መጻሕፍትን አስተርጉመዋል፤ ከዚያ ቀደም የደረሷቸውን መጻሕፍት በብዛት አሳትመው አሰራጭተዋል፤ አዳዲስ መጻሕፍትንም ደርሰው ለሕትመት አብቅተዋል።

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ከእስር በፊት ለማዕረገ ጵጵስና ተመርጠው እየተዘዋወሩ ሥራ ለመሥራት ከነበራቸው ፍቅር የተነሳ ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ነገር ግን በ-1983 ዓም ከቅዱስ ሲኖዶስ በተላኩ 3 ሊቃነ ጳጳሳት ምልጃ የጵጵስና ማዕረግ ቢቀበሉ በሲኖዶሱ ነግሶ የነበረውን መለያየት በማርገብ ሊረዷቸውን እንደሚችሉ እንዲሁም ደግሞ በውጭ ሆነው ከሚያግዙት ይልቅ በውስጥ ሆነው ቢሰሩ አሰራሩንንም ሊያሻሽሉላቸው እንደሚችሉ ስለተነገራቸው እና ብፁዕነታቸውም ስላመኑበት በዚሁ ዓመት ጥቅምት 18 በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ አባ መልከ ጼዴቅ ተብለው ማዕረገ ጵጵስናን ተቀብለዋል።

ብዙም ሳይቆይ በሀገሪቱ የመንግሥት ለውጥ ሆነና ቤተ ክርስቲያኗ በአዲሱ መንግሥት እጅ ወደቀች። ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም የሚደርስባቸው ማስፈራራት ሳያንስ በኃይል ተገደው ከመንበሩ እንዲወርዱ እና ሲኖዶሱ በታጣቂ ጳጳሳት ስር እንዲሆን ተደረገ። ይህም ሳያንስ ሕግ ፈርሶ እና ቀኖና ተጥሶ የመንበረ ፓትርያሪክም ክብር ወርዶ እና ተዋርዶ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በሕይወት እያሉ ሌላ ሕጋዊ ያልሆነ ፓትሪያሪክ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ተሾመ። ከተራ ዲያቆን ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ እውነተኛ ሠራተኞች ከስራ እየተፈናቀሉ በምትካቸው ካድሬዎች ቤተ ክርስቲያኗን ሞሏት። አዲሱን የፓትርያሪክ ሹመት የማይቀበሉ እና ከወታደራዊው ሲኖዶስ ጋር አብረው የማይሠሩ ጳጳሳትም ሆኑ ካህናት እንግልት እንደሚደርስባቸው ማስፈራሪያው እየበዛ መጣ። ሀገሪቱም ቤተ ክርስቲያኗም ተያይዘው አደጋ ላይ ወደቁ። በዚህ ሀገርን የማፍረስ፣ ቤተ ክርስቲያንን የማዋረድ፣ ታሪክን የማጥፋት እና ትውልድን የመግደል ዘመቻ ላይ ለመሳተፍም ሆነ ይህ ሲከናወን ለማየት ያልወደዱት ብፁዕነታቸው በሀገር ውስጥ ሆነው በተለያየ መልኩ አውግዘው ሲጽፉ እና ሲናገሩ ሰሚ ስላልነበረ ሃሳብን በነጻ መግለጽ ወደሚቻልበት ሀገር የሚወዷትን ሀገር ጥለው ተሰደዱ። 

ምንም እንኳን ከሚወዷት ሀገር በመለየታቸው ስደት ይባል እንጂ ስደታቸው ለበረከት ሆኖላቸው “ለእግዚአብሔር ምድር በምልዓ=ምድር እና መላዋ የእግዚአብሔር ናት” እንዲል ነቢዩ እግራቸው የረገጡት መሬት ሁሉ ሀገራቸው ሆኖላቸው በአሜሪካ በየግዛቱ እየዞሩ ሐዋርያዊ ተግባር በማከናወን ሕዝቡን ለመሰብሰብ እና ለማስተማር ችለዋል። ቅዱስ ፓትርያሪኩ በስደት ወደ አሜሪካ እስኪገቡ ድረስ ስደተኛውን ሕዝብ እያጽናኑ ቆይተው ከቅዱስ ፓትርያሪኩ መምጣት በኋላም ሕጋዊው ሲኖዶስ በአሜሪካ ሥራውን ሲቀጥል በጸሐፊነት እንዲሠሩ ተመርጠው ሲኖዶሱና ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ከነሙሉ ክብራቸው ወደ መንበራቸው እስከተመለሱበት ሐምሌ 2010 ዓም ድረስ በትጋት አገልግለዋል። መንበራቸውን በበርክሊ በኋላም በኦክላንድ መድኃኔ ዓለም አድርገው በመላው ክፍለ ዓለማት እየዞሩ አብያተ ክርስቲያናተን አሳንፀዋል፤ ምዕመናንንም ሰብስበዋል። ምንም እንኳን ሀገረ ስብከታቸው ካሊፎርኒያ ይሁን እንጂ በመላው አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ እና አፍሪካ በመዘዋወር በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ምስረታ ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል። ማታ በምዕራብ ታይተው ጠዋት በምስራቅ ለአገልግሎት የሚገኙት ብፁዕ አባታቸን መኖርያዎት የት ነው ብሎ ለሚጠይዋቸው ሁሉ “አየር ላይ” እስኪሉ ድረስ ሌሊት በጉዞ አድረው ያለ ምንም ድካም ጠዋት ላይ አገልግሎት ላይ ሲታዩ ፊታቸው ከድካም ይልቅ ትጋት የሚታይበት አባት ነበሩ። በስደት ለነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ ዕድገት ያለድካም እና ያለመሰልቸት ይሠሩ ስለነበር በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር የሚተደዳሩ አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ይገኝ ነበር፤ ከአብያተ ክርስቲያናቱ መብዛትም የተነሳ ጳጳሳት በማስፈለጋቸው ሁለት ጊዜ የጳጳሳት ሹመትን ለቅዱስ ሲኖዶስ እያቀረቡ በርካታ ጳጳሳትን ለማሾም ችለዋል። ከብፁዕነታቸው ሐዋርያዊ አገልግሎትም የተነሳ በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚተዳደሩ አብያተ ክርስቲያናት ንጹሕ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ከምንም ጋር ሳይቀላቀል እንዲሰበክ እና ምዕመናን እንዲታነፁበት ሁኗል።

በመላው ዓለም በተለይም ደግሞ በካሊፎርኒያ ግዛት ምዕመናን ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ፣ በጥሩ ሥነ ምግባር እንዲታነፁ፣ ጠንካራ ሠራተኞች እንዲሆኑ፣ ልጆች በመልካም ጎዳና እንዲያድጉ ጠንክረው በመሥራታቸው እና ለተገፉት ድምፅ በመሆናቸው እንዲሁም ስለነጻነት በአደባባይ በመናገራቸው በካሊፎርኒያ ግዛት ከሚገኙት ከኦክላንድ፣ በርክሊ፣ ሳንፍራንሲስኮ፣ ሳንሆዜ፣ ሳንታክላራ ከተሞች ከንቲባዎች፥ ከሶስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፥ ከሁለት የጉባኤ አባላት፥ እና ከካሊፎርኒያ የሸንጎ አባላት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። ከፍተኛ የሕይወት ተሸላሚ በመሆናቸውም የትውልድ ቀናቸው ሐምሌ 12 (July 19) የአቡነ መልከ ጼዴቅ ቀን ሆኖ ተሰይሞላቸዋል። በሕይወት ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦ ይመጥናል ባይባልም መታሰቢያቸው ይሆን ዘንድ አንድ ቤተ-መጻሕፍት በስማቸው የተቋቋመው የመልከ ጼዴቅ ፋውንዴሽን አባላት እና የኦክላንድ መካነ ሰላም መድኃኔ ዓለም አስተዳደር ቦርድ በወሰኑት መሠረት ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓም(May 12,2018) ብፁዕነታቸው እና መላው የሲኖዶሱ አባላት ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ተመርቆ ተክፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ይህም ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መላ ሕይወታቸውን እና ሕያው ሥራቸውን በግልፅ የሚያሳይ እና ትውልድ ሊማርበት የሚችል ቋሚ ቅርስ ነው።

ብፁዕነታቸው በስደቱ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት እየተስፋፉ፣ ያመኑት ሕዝብ ዕለት ዕለት እየበዙ፣ ወንጌል በምልዓት እና በስፋት እየተሰበከ፣ ከብድር እና ከዕዳ ነጻ የሆኑ ታላላቅ ካቴድራሎች እየተሠሩ ማየታቸው እያስደሰታቸው ቢኖርም የቤተ ክርስቲያን ከሁለት እና ከሶስት መከፋፈል እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስ በስደት መኖር በጥብቅ ያሳስባቸው ነበር። ሲኖዶሳዊ አንድነቱን ለማየት ያላቸውን ጉጉት በመጽሐፋቸው “እግዚአብሔር አቆይቶኝ የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖናዊ አንድ አስተዳደር እንደቀድሞው ሲሆን ለማየት ያበቃኝ ይሆናል” ሲሉ ገልጠውታል። ይህ ምኞታቸውም እንዲሳካ በቅዱስ ሲኖዶስ የዋና ፀሐፊነት ዘመናቸው በአራት የዕርቀ ሰላም ድርድሮች ላይ ሕጋዊውን ሲኖዶስ በመወከል እና የኮሚቴው ዋና ፀሐፊና ሰባሳቢ በመሆን ሠርተዋል። ከ-July 23-28, 2018 በዋሽንግተን ዲሲ የተደረገውን የመጨረሻውን የዕርቀ ሰላም ጉባኤ በሃላፊነት መርተዋል። በዚህም ጉባኤ ውህደቱ በመሳካቱ የተሰማቸውን ደስታ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር በተገኙበት “የዛሬ 27 ዓመት በግፍ ከሀገር ያስወጣን መንግሥት ይሄው ዛሬ በክብር ወደ ሀገራቸን ሊመልሰን ነው” ሲሉ ገልፀዋል።  ከውህደቱም በኋላ ሳይውሉ እና ሳያድሩ ቅዱስ ፓትርያሪኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ ከጠቅላይ ሚንስቴሩ ጋር ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ብፁዕነታቸው በነበረባቸው ሕመም ምክንያት አብረው ሊገቡ አልቻሉም ነበር።

ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ ታኅሣሥ 22,2010 (December 30,2018) በውህደቱ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለፅ ከ-27 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደሚወዷት ሀገር ገብተዋል።  በዚህም ጉዟቸው ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በመኖሪያ ቤታቸው ሄደው የደስታ መልዕክታቸውን ሲያደርሱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ግን “የለም እኔ ነኝ ወደ እርሰዎ መምጣት ያለብኝ እንጂ እርሰዎ ወደእኔ መምጣት የለበወትም” በማለት በብፁዕ አባታችን ማሪፊያ ቦታ ከበርካታ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ተገኝተው ሰላምታ አቅርበውላቸዋል። ከዚያም በኋላ በግንቦት ወር 2010 በተደረገው የርክበ ካህናት ስብሰባ ላይ የጤንነታቸው ሁኔታ ሳያግዳቸው ተገኝተው ለቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት አባታዊ ምክራቸውን ለግሰው ተመልሰዋል።

ከዚህም ጊዜ በኋላ ምንም እንኳን ከባድ ሕክምና እየተደረገላቸውም ቢሆንም ደከመኝ ሰለቸን ሳይሉ ቤተ ክርስቲያንን የማገልገሉን እና ምዕመናኑን የማጽናናት ስራቸውን ቀጥለውበት ነበር። ከቦታ ቦታ መዘዋወር ከባድ ቢሆንም ቅሉ ብፁዕነታቸ ደጋግመው ተገኝተው ባገለገሉበት ዳላስ ደብረ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በህዳር 2012 ዓም ተገኝተው አዲሱን የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት መርቀው ከፍተዋል። ይህ ትምህርት ቤትም በቀላል መታየት የሌለበት እና ትውልዱ ሁሉ ሊማርበት የሚገባ መሆኑን አስገንዝበው እና አባታዊ ምክራቸውንና ቡራኬያቸውን ሰጥተው ተመልሰዋል።

በጠቅላላው ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ፍኖተ እግዚአብሔርን ተከትለው መላ ዘመናቸውን ሕዝባቸውን፣ ቤተ ክስቲያናቸውን እና ሀገራቸውን በቅንነት እና በእውነት ሲያገለግሉ የኖሩ ለጋስ እና ደግ አባት ነበሩ። ብፁዕነታቸው ስለእውነት የኖሩ፣ ሰላምን አጥብቀው የሚሹ፣ ሐዋርያዊ ተግባራቸውን ሳይፈሩ ያከናወኑ፣ ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን መከበር የሠሩ እና ያሠሩ አባት በመሆናቸው ሲታወሱ ይኖራሉ። አቡነ መልከ ጸዴቅ ከአማርኛ እና ከግዕዝ በተጨማሪ እንግሊዝኛ፣ ግሪክ፣ ቱርክኛ፣ አረብኛ እና መጠነኛ ትግርኛ ቋንቋዎችን መናገር የሚችሉ ልዩ ሀብተ ልሳን የተሰጣቸው አባት ከመሆናቸው የተነሳ በተለያዩ ዓለማት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በልዩ ልዩ ዓለማቀፍ መንፈሳዊ ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ ችለዋል። በቤተ ክርስቲያናቸን ሊቃውንት ነበሩ ተብሎ በነበር የቀሩ፥ እነርሱንም ዕውቀታቸውንም አፈር የበላው ብዙዎች ሲሆኑ ብፁዕነታቸው ግን ዕውቀታቸውን ትውልድ ይማርበት ዘንድ እስካሁኑ ጊዜ ድረስ 22 መጻሕፍትን ደርሰው ለንባብ አብቅተዋል፤ ብዙዎቹ መጻሕፍትም እንደልጃቸው በሚቆጥሩት በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ቤት ማስተማሪያ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያትም ወደ 11 የሚደርሱ ያልታተሙና ወደፊት ታትመው ለምዕመናን የሚሰራጩ መጻሕፍቶችን ደርሰዋል። ብፁዕነታቸው የቤተ ክህነት ትምህርት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የጊዜ ምንነት እና ጥቅም የገባቸው ስለነበሩ በእስር ቤት እንኳን ሳይቀር ምንም ጊዜ ሳያባክኑ መላ ዘመናቸውን ሲያነቡ፣ ሲጽፉ፣ ሐዋርያዊ ተግባር ሲያከናውኑ የኖሩ እና ምዕመናን ልጆቻቸው የሚኮሩባቸው ምሉዕ አባት ነበሩ።

በረከታቸው ይደርብን። አሜን!